2016 ዲሴምበር 8, ሐሙስ

ስለ 666 ያውቃሉ?



             ንቁ
WAKE UP! | ንቁ!!!
ህ ዜና ምናልባት ለሁላችንም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ነው። መቶ በመቶ የተረጋገጠ እኛ የመጨረሻው   ዘመን ኗሪዎች ነን። ብዙ ምልክቶች በዓለማችን ላይ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም መምጣትን አሳውቀውናል። እንደታሪክም ተወርቶልናል። አውርተናል፣አይተንማል። ሰምተናቸው ረስተናቸውም አልፈናል። በማቲዎስ ወንጌል 16፥3 ላይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለተሰበሰበው ህዝብ እርሱ ተመልሶ ሲመጣ የሚከሰቱትንና የሚታዩትን ምልክቶች ሲነግራቸው፣ ስላላስተዋሉ ሲነቅፋቸው እናነባለን። “ማለዳም ሰማዩ ደምኖ ቀልቷልና ዛሬ ይዘንባል ትላላችሁ። የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችሁ፤የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን?”  እርሱም መጀመሪያ ምልክትን ከእርሱ በመጠየቃቸው አዝኖባቸው ነበርና ብዙ ሰዎች ዛሬ ላይ የራሳቸውን ዓለም ተከትለው ወድቀዋል። ሰዓቱንና ጊዜውን ስላላወቁት የትኛውን ህይዎት እንደሚኖሩት እንኳን ሳያውቁት ጠፍተው ቀርተዋል።
በኖኅና በሎጥ ዘመን እግዚአብሔር ለህዝቡ የማስጠንቀቂያ ምልክትን ብዙ ጊዜ አስተላልፎ ነበር። የሚመጣውን ቁጣና ፍርድ እንዲያመልጡ ብዙ ግዜ ታግሶ ነበር። ነገር ግን ሊሰሙትና ከኃጢያታቸው ሊለዩ ፈቃደኛ አልነበሩም። እንደውም በራሳቸው ማስተዋልና እውቀት ተደግፈው የእግዚአብሔርን የቁጣ ማስጠንቀቂያ ቃል ችላ በማለት ናቁት። ነገር ግን ሳያስቡት የእግዚአብሐር የቁጣ ፍርድ መቅሰፍት ደረሰባቸው። በዚያ ጊዜ ህዝቡ ተዘናግቶ ሳይዘጋጅ እግዚአብሔር መቅሰፍትን አመጣ። ልክ እንደ ኖኅ ዘመን ዛሬም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ እንዲሁ ይሆናል። በኖኅ ዘመን እንደሆነ ሁሉ በሰው ልጅም ዘመን እንዲሁ ይሆናልና። ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ድረስ ይበሉና ይጠጡ ያገቡና ይጋቡም ነበር። የጥፋት ውኃም መጣ ሁሉንም አጠፋ። እንዲሁም በሎጥ ዘመን እንደሆነ ይበሉና ይጠጡ ይሸጡም ይገዙም ነበር። ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ፡ ሁሉንም አጠፋ።
የሰው ልጅ[1]  በሚገለጥበትም ቀን እንዲሁ ይሆናል። ሉቃስ 17፥26-30 ሁላችንም እየኖርን ያለነው በመጨረሻው ዘመን ቀን ላይ ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም በሚገለጥበት ጊዜ አስቀድሞ የሚከሰቱ ብዙ ምልክቶች እንዳሉ ራሱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል። ከተናገራቸውም የትንቢት ቃሎች ብዙዎቹ ተፈጽመዋል፤ በመፈጸምም ላይ ናቸው። ለምሳሌ፦ በዓለማችን የ1ኛውንና የ2ኛውን የዓለም ጦርነቶች ጨምሮ እስካሁን ድረስ በዓለማችን ላይ ብዙ መቶ ሚሊዮን ህዝብ ያለቁባቸው ጦርነቶችና ግጭቶች ተካሂደዋል። እንዲሁም በተለያዩ በሽታዎችና ምክንያቶች በተለያዩ ጊዜያት እስካሁን ድረስ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ህይዎቱን አጥቷል። በተጨማሪም በዓለማችን ላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ህይዎቱን በርሃብ አጥቷል። በዓለማችን ላይ በመሬት መንቀጥቀጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ህይዎቱን አጥቷል። ህዝብ በህዝብ ላይ መንግስትም በመንግስት ላይ ይነሳልና በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ርሃብም ይሆናል። እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያዎች ናቸው (ማር 13፥8)። ሌላው ደግሞ በመጨረሻው ዘመን የትንቢት ሌላኛው ምልክት የሆነው ለዓለም ህዝብ በሙሉ አልሰማሁም፣ አላየሁም፣ አላወቅሁም እንዳይል ወንጌል ይሰበካል። በአሁኑ ጊዜ ባለው የመረጃ አሀዝ መሰረት ወንጌል ከ95% በላይ በዓለም ላይ ተሰብኳል፤ እየተሰበከም ነው። ለዚህም ለወንጌል መፋጠን የኤሌክትሮኒክስ አውታሮች ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ይላል፤ አስቀድሞ  ወንጌል ለአህዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል (ማቲ 13፥11)።
ነገር ግን በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ እርቅን የማይሰሙ፣ ሀሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከሀዲዎች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ። የአምልኮ መልክ አላቸው፤ ኃይሉን ግን ክደውታል። ከዚህ ደግሞ እራቅ። ወደቤቶች ሾልከው እየገቡ ኃጢያታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞት የሚወሰዱትንም ሁሉ ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩትም ከእነርሱ ዘንድ ናቸውና (2ኛ ጢሞ ምዕራፍ 3)።
ሌላኛው በመጨረሻው ዘመን እንደሚሆን በትንቢት የተነገረው የ666 ምልክትን መቀበል ነው። በአሁኑ ሰዓት በአውሮፓና አሜሪካ የገንዘብ መገበያያ ካርዶች፣ መታወቂያ ካርዶች፣ መንጃ ፈቃድ፣ ፓስፖርት በሙሉ ዲጂታል ኮምፒውተራይዝድ ኤሌክትሮኒክስ[2] ሲሆኑ በአሜሪካ አገር ለሙከራ ተብሎ የማይክሮ ችፕስ 666 ምልክትን በፈቃደኝነት መቀበል ከተጀመረ ቆይቷል። በግራ እጅ ላይ የሚቀበረው የማይክሮ ችፕ እስከ 2017 እ.ኤ.አ. ለሁሉም አገልግሎት ተግባባራዊ እንዲሆን የኦባማ አስተዳደር መመሪያ ማስተላለፉም አይዘነጋም። በ2017ም እኤአ 30 ሚሊዮን የሚጠጋ የማይክሮ ችፕ በግዙፉ የማይክሮ ሶፍት ኩባንያ አይቢኤም (IBM) በኩል ተመርቶ በተባበሩት መንግስታት በኩል እንዲሰራጭ በማድረግ በዓለም ላይ ያሉ የሰው ልጅን ጨምሮ የቤት እንስሳት በሙሉ እንዲዎስዱት ይደረጋል። ለዚህም ደግሞ ልዕለ ኃያሏ አገር አሜሪካ ዝግጅቷን ጨርሳለች። ይህ ጊዜም እጅግ ከባድ ነው። ምክንያቱም ምልክቱን አንዴ የተቀበለ መመለስ ስለማይችል ደግሞም አልቀበልም ያለ መግዛት፣ መሸጥ፣ መበደር፣ መክፈል አይፈቀድለትም፤ እንዲሁም ፓስፖርት፣ ክሬዲት ካርድ፣ መንጃ ፈቃድና የማንነት መታወቂያ ማግኘት አይችልም። በአጠቃላይ 666 ማይክሮ ችፕን ያልተቀበለ በዓለም ላይ መኖር አይችልም። የጻድቃን የፈተና ፅናት በዚህ ይታወቃል።  ታናናሾችና ታላላቆችም፣ ባለጠጎችና ድሆችም፣ ጌቶችና ባሪያዎችም ሁሉም በቀኝ እጃቸው ወይም በግራ እጃቸው አሊያም በግንባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፤ የአውሬውንም ስም ወይም የስሙ ቁጥር (666) ያለውን ምልክት የሌለበትን ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ። አዕምሮ ያለው የአውሬውን ቁጥር ይቁጠረው፤ ቁጥሩም የሰው ቁጥር ነውና። ቁጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው (የዮሃንስ ራዕይ 13፥16-18)።
የትንቢቱ የመጨረሻ ደወል የሆነው ደግሞ የእስራኤል በጭፍና መወረርና ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን የጎግ ማጎግ ጦርነት እንዲሁም ሀሰተኛው የክርስቶስ ተቃዋሚ በዚህ በታላቁ ቀን ጦርነት የሚገለጥ ሲሆን ይህ ጦርነት እግዚአብሔር የያዕቆብን ጠላቶች በፉጨት የሚጠራበትና ኃይሉን፣ ክብሩን፣ ማንነቱን የሚያሳይበት ጦርነት ነው። በዚህ ጦርነት እስራኤልን ለመውጋት ከዓለም የተውጣጣና የተዘጋጀ ጦር የእግዚአብሔርን የፉጨት ጥሪ ሲሰማ ከያለበት ቦታ ተነስቶ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ እየሩሳሌም ይሰበሰባል። በዚያም ከተማዋን ይከባል። በመጨረሻም በእግዚአብሔር የተደገሰለትን የሞት ድግስ ይበላል፣ ይጠጣልም። በዚህ የሞት ድግስ ላይም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሟቾቹ ጋር ትጋበዛለች። በመጽሐፍ ቅዱስ በትንቢተ ሕዝቅኤልና በዮሀንስ ራዕይ የተነገሩትን የትንቢት ቃሎች የመጨረሻውን ዘመን በማስመልከት የዓለም ፍጻሜ የሆነውን የታላቁን የእግዚአብሔርን ቀን በሕዝቅኤል 38 እና 39 እንዲሁም በራዕይ 16 የተገለጠውን የጎግ ማጎግን ጦርነት የትንቢቱ ቃል መፈጸሚያ የሆነችውን እስራኤልን ሊወጉ በየአራቱም አቅጣጫ እስራኤልን የሚከቧት አገሮችና በዋነኛነት ጦርነቱን በግንባር ቀደምነት የሚመራው አገር ጎግ ማጎግ የሚባለውና እስራኤልን የሚወጋው የትንቢቱ ቃል ከዚህ ቀደም በዓለምላይ ይህንን የትንቢት ቃል የማያውቁ ክርስትያኖች በአብዛኛውም ዘንድ (የሁሉም ግምት ማለት በሚቻል ሁኔታ) ሩሲያ ነው። ጎግማጎግ ብሎ በማመን ወደ ድምዳሜው ተደርሶ ነበር። ነገር ግን ሩሲያ የክርስትያን ሀገር ነች። ክርስትያን ሆኖም እስራኤልን የሚወጋ የለም ይለናል ጥናቱ። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የተፃፈውን ቃል በጥንቃቄ ስናጠናውና ስንመረምረው ወደ ዛሬው ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል። ጦርነቱ ምናልባት በሀይማኖት ልዩነት ሳይሆን በፖለቲካ ተቃርኖ ምክንያት ሊጀመር ይችላል። እንደምታውቁት አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ሊፈታ የማይቻል ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ ነች። እስራኤል ደግሞ የአሜሪካ አጋር ናት። ስለዚህ እስራኤልና ሩሲያ በተቃራኒ ጎራ ይመደባሉ። አዎ እውነት ነው። ያ የፍፃሜ ቀን ደርሷል። ትንቢቱ ሁሉ ተፈጽሟልና። አውሬውም እንደ ተራበ አንበሳ እየጮኸ ነው። እንዳይበላን ዛሬውኑ እንንቃ። በኖኅና በሎጥ ዘመን እንደጠፉት ህዝቦች እንዳንጠፋ ከደጁ ሄድን እንጩህ። መሐሪ ነውና ይምረን ዘንድ እንዳስተማረን ንስሀ እንግባ።
ንቁ!!! በአብ ቀኝ ተቀምጦ የሚፈርደው፣ ስለኛ በመስቀል ላይ የተሰቀለው፣ ከድንግል ማርያም የተወለደው፣ የእግዚአብሄር ልጅ ኢየሱስ ከነገር ሁሉ ያድናል። ጌታ ኢየሱስ ተመልሶ  ይመጣል። ማራናታ።
አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና!
ዳንኤል ገብረ ማርያም
ህዳር ፳፻፱ ዓመተ ምህረት
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
እግዚእ-አብ-ሔር በቸርነቱ ከጥፋት ሁሉ ይጠብቀን። አሜን።


[1] የሰው ልጅ ሚለው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው።

[2] ዲጂታል ኮምፒውተራይዝድ ኤሌክትሮኒክስ የሚለውን ሀረግ ሊተካ የሚችል የአማርኛ ቃል ስላላገኘሁ ነው የእንግሊዝኛውን ቃል የተጠቀምሁ